በሞቃዲሹ በመንግሥት ወታደሮች እና በተቃዋሚዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ በመንግሥት ወታደሮች እና በተቃዋሚ ታጣቂዎች መካከል በምርጫ መዘግየት ምክንያት የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተሰማ።
ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ የሥልጣን ዘመናቸው ግንቦት 7/2018 ዓ.ም. ቢያበቃም በአንድ ዓመት ተራዝሞላቸው ነበር።
ተቃዋሚዎች የሥልጣን ጊዜው መራዘሙን ኢ- ሕገመንግሥታዊ ሲሉ በመጥራት ሐሙስ ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተው ነበር።
በዋና ከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ከትናንት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ነዋሪዎች ሌሊቱን ቀጥሎ ማደሩን ተናግረዋል።
ፖሊስ በተወሰኑ አካባቢዎች "የሞርታር ጥቃት በፈጸሙ እና በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ" ታጣቂዎች ላይ "መጠነ ሰፊ የጸጥታ ዘመቻ" እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
የፕሬዚዳንቱ የሥልጣን ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ እና ተቃዋሚዎች ንግግር ቢጀምሩም ውጤት ሊያመጣ አልቻለም።
ፕሬዚዳንት ሞሐሙድ ሶማሊያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለመውሰድ በሚል የጎሳ መሪዎች ተወካዮቻቸውን ከሚመርጡበት ሥርዓት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማድረግ ወደሚያስችል ሥርዓት ለመቀየር ጥረት እያደረጉ ነው።
ሶማሊያ አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚል ምርጫ ያካሄደችው እአአ በ1969 ሲሆን ከዚያ በኋላ ባለፉት 30 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሳን አሊ ካሃይሬ ሐሙስ ዕለት ለሚያካሄዱት ሰላማዊ ተቃውሞ ከሌሎች ጋር በመሆን እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት የመንግሥት ወታደሮች ጥቃት እንደፈጸሙባቸው ተናግረዋል።
"በዚህ ክስተት ምክንያት ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት ወይም ውድመት ተጠያቂው የሥልጣን ዘመናቸው ያበቃው ፕሬዝዳንት ናቸው"ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
"ይህ ጥቃት የሶማሊያ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ላይ የተፈፀመ ከባድ ጥቃት እና ሆን ተብሎ ሰላማዊ ሰልፍን ለማፈን የተደረገ ሙከራ ነው" ሲሉ አክለዋል።
እስካሁን ድረስ በተኩስ ልውውጡ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ያልታወቀ ሲሆን ፕሬዝዳንቱም ምንም አስተያየት አልሰጡም።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሼክ አህመድ በኤክስ ገጻቸው ላይ ሁከቱ የታቀዱትን ሰልፎች እንደማያስቆም ተናግረዋል።
"ፕሬዝዳንቱና ወታደሮቹ እንደምንፈራ ወይም እንደምንሸሽ ካሰቡ አንሸሽም" ብለዋል።
ሞቃዲሾ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጥቃቱን "ግድየለሽነት የተሞላበት" ሲል ገልጾ በሁሉም ወገን ያሉ መሪዎች "መረጋጋትን የማስቀጠል እና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ኃላፊነት አለባቸው" ብሏል።















