በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጡት ካንሰር ሕሙማን ኬሞቴራፒን በጥንቃቄ ሊያስቀሩ የሚችሉበትን መንገድ አንድ ጥናት ጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጡት ካንሰር ሕሙማን በጥንቃቄ ኬሞቴራፒን ሊያስወግዱ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ተመራማሪዎች ተናገሩ።
ተመራማሪዎች በኬሞቴራፒ ሊጠቀሙ የሚችሉ እና የማይጠቀሙ ሕሙማንን ለመለየት የሚያስችል የዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ የሰሩ ሲሆን የሙከራው ውጤቱንም ይፋ አድርገዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ ጥናት በምርምሩ ላይ ከተሳተፉ ሁለት ሦስተኛው የኬሞቴራፒን የጎንዮሽ ጉዳት ማስቀረት እና በሆርሞን ቴራፒ መታከም እንደሚችሉ ተደርሶበታል።
የኬሞቴራፒ ሕክምና ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ የፀጉር መርገፍ፣ የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም እና የመውለድ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።
በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን (ዩሲኤል) የሚመራው ይህ ጥናት በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ አውስትራሊያ፣ ኒውዚላንድ እና ታይላንድ ውስጥ ከ4,000 በላይ አዲስ በጡት ካንሰር መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጡ ታካሚዎችን አካትቷል።
ሳይንቲስቶች በጡት ካንሰር እድገት ውስጥ ሚና ያላቸውን 50 ዘረመሎችን (ጂኖችን) እንቅስቃሴ ለመለካት እና የታካሚውን የበሽታው የመመለስ አደጋ ለማስላት ፕሮሲግና (Prosigna) የተባለ ምርመራን ተጠቅመዋል።
ዝቅተኛ ውጤት ያገኙት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ የቡድኑ አባላት የኬሞቴራፒ ሕክምና አልተሰጣቸውም። እነዚህ ሕሙማን ለአምስት ዓመት ክትትል ተደርጎላቸው የኬሞቴራፒ ሕክምና ከወሰዱት ታካሚዎች መካከል ጋር ሲነጻጸሩ 93.7 በመቶ የመዳን ዕድል እንዳላቸው ታኣውቋል።
ይህም የኬሞቴራፒ ሕክምናቸውን ተከታትለው ከዳኑት 94.9 በመቶ የሚሆነው መጠን ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ልዩነት ያለው ሆኖ ተገኝቷል።
የጡት ካንሰርን ለማከም ዋናው ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ በቀዶ ሕክምና ዕጢዎችን ማስወገድ ነው። ከዚያ በኋላ የመታመም አደጋ ለመቀነስ ብዙውን ጊዜ ኬሞቴራፒ ይታዘዛል።
አብዛኛውን ጊዜ ሕክምናው የሚታዘዘው የመጀመርያ ደረጃ ጡት ካንሰር ላለባቸው እና በአቅራቢያው ወደሚገኙ ሊምፍ ኖዶች የተዛመተ ከሆነ ነው።
ተመራማሪዎች ሕክምናው በጣም የተለመደ የጡት ካንሰር ላለባቸው ሰዎች ብዙም ጥቅም ላይሰጥ እችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ዩሲኤል ተናግሯል።
ዩኒቨርሲቲው ከሙከራው በኋላ በዓመት ከ5,000 በላይ የኤን ኤች ኤስ ታካሚዎች የኬሞቴራፒ ሕክምናን ማስቀረት እንደሚችሉ ተናግሯል።
ከካርዲፍ የመጣችው ካረን ቦንሃም በሙከራው ላይ የተሳተፈች ሲሆን ውጤቶቹ "እጅግ በጣም እፎይታ" እና "ዳግም የመወለድ" ስሜት እንዲሰማት ማድረጉን ተናግራለች።
የ64 ዓመቷ አዛውንት በፕሮሲግና ምርመራ ምክንያት የኬሞቴራፒ ሕክምናን ማስቀረት የቻለች ሲሆን በምትኩ ለስምንት ዓመታት የራዲዮቴራፒ እና የሆርሞን ቴራፒ ሕክምና ወስዳለች።
"የካንሰር ምርመራና ሕክምና አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል" የሚሉት አዛውንቷ "እርግጠኛነት ወደጠፋበት ዓለም ይገፋሃል። በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንደገና ማስተካከል፣ በሕይወት መትረፍ ብቻ ነው የምትፈልገው።"
የጥናቱ ግኝቶች ቅዳሜ ዕለት በዓለም ትልቁ የካንሰር ጉባዔ በሆነው እና በቺካጎ ዩናይትድ ስቴትስ በሚካሄደው የአሜሪካ ክሊኒካል ኦንኮሎጂ ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ይቀርባሉ።
የጥናቱ ዋና ተመራማሪ እና በዩሲኤል የካንሰር ተቋም የጡት ካንሰር ፕሮፌሰር የሆኑት ሮብ ስታይን "እነዚህ ውጤቶች በግለሰብ ደረጃ የተበጀ ሕክምናን አስፈላጊነት እና ጉልህ እርምጃን ያመለክታሉ።
"ሙከራው በባህላዊ ክሊኒካዊ ባህሪያት ላይ ብቻ ከመመስረት ይልቅ የዕጢው ጄኔቲካዊ እና ሞለኪውላር ሁኔታዎችን በመመልከት ውሳኔዎችን ለመስጠት በተሳካ ሁኔታ ተጠቅሟል።"
"ለብዙ ታካሚዎች የኬሞቴራፒ አካላዊ እና ስሜታዊ ጫና እና የረጅም ጊዜ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንዲያመልጡ ያደርጋል"
"ለጤና ስርዓቶች የበለጠ ቀልጣፋ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የሀብት አጠቃቀምን ይወክላል።"
እንደ ዩሲኤል ዘገባ ግኝቶቹ ከ40 ዓመት በታች ለሆኑ ሰዎች የሚያገለግሉ ስለመሆናቸው ገና ብዙ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል።















