አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ አነሳች

የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መነሳቱን አሜሪካ አስታወቀች። ማዕቀቡ መነሳቱን የገለፀው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር መከላከያ ንግድ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ነው።

ዳይሬክቶሬቱ ሰኞ ግንቦት 3/2018 ዓ.ም. እንደገለጸው በኢትዮጵያ ላይ ይከተል የነበረውን የክልከላ ፖሊሲ በማንሳት አሁን ላይ በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ዝውውር ደንብ (ITAR) ቁጥጥር የሚደረግባቸውን እና ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ የፈቃድ ማመልከቻዎችን በየተራ እየገመገመ ነው።

ይህን ተከትሎ በቅርቡ በሚወጣ የደንብ ለውጥ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ዝውውር ደንብ - ITAR 126.1 ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙ አገራት ተርታ "እንድትሰረዝ" የሚደረግ መሆኑን ጠቅሷል።

ይህ ደንብ፣ በአሜሪካ ማዕቀብ ስር የሚገኙ የተወሰኑ አገራት፤ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ፣ ለደህንነት እና ለሌሎችም የአገር ውስጥ የጸጥታ ኃይሎቻቸው የሚሆኑ የመከላከያ ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን ከውጭ ገዝተው ማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ አገራት መላክ እንዳይችሉ የሚከለክል ነው።

ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው የትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከኅዳር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከ4 ዓመታት በላይ በዚህ ማዕቀብ ውስጥ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት የጦር መሣሪያ በብዛት የጦር መሣሪያ የምትገዛው ከሩሲያ፣ ቻይና፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ኢራን መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

አሜሪካ ጥላ የነበረው ማዕቀብ መነሳቱ ይፋ የሆነው በኢትዮጵያ ግጭቶች በቀጠሉበት እና የትግራይ ክልል ውጥረት ባየለበት፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ውጥረት ባለበት ወቅት ነው።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የጦር መሳርያ ማዕቀብ ለማንሳት ከውሳኔ ላይ የደረሰችበትን ምክንያት በይፋ አልገለጸችም።

ሆኖም የአሜሪካ መከላከያ ንግድ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ይህ ማዕቀብ መነሳቱን ይፋ ያደረገው፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ወደ ዋሽንግተን አቅንተው ከአሜሪካው አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ ጋር በሁለትዮሽ እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው፤ በምሥራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመፍታት እና ውጥረቶችን በማርገብ ረገድ ኢትዮጵያ "በምትጫወተውን ወሳኝ ሚና" ላይ አጽንኦት ሰጥተው መነጋገራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። በተጨማሪም የሁለቱ አገራት የጸጥታ አጋርነት፣ እንዲሁም የአገራቱን የንግድ ዕድሎች ማሳደግ፤ "ቀይ ባሕር እና የማሪታይም ደኅንነት" ጉዳዮች ውይይታቸው የዳሰሷቸው ነጥቦች ናቸው።

ማርኮ ሩቢዮ ከዶ/ር ጌዲዮን ጋር በአካል ተገናኝተው ከመነጋገራቸው አስቀድሞ፤ በዚያው ዕለት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በቀጠናዊ መረጋጋት፣ በጸረ-ሽብር ትብብር፣ በኢኮኖሚ እና በአፍሪካ ቀንድ ደህንነት ዙሪያ በስልክ ተወያይተዋል።

የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቀይ ባሕርን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመወያየታቸው እና በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሳርያ ማዕቀብ ከመነሳቱ ጥቂት ቀናት አስቀድማ አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ለማንሳት ማቀዷ መዘገቡ ይታወሳል።