'እንዲሁ ተነስቼ መጮኽ ብጀምርስ?' – ድንገት ወደ አዕምሯችን ስለሚመጡ ረባሽ ሃሳቦች መስጋት ያለብን መቼ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቤተሰብ፣ የስራ ወይም ቀበሌ ስብሰባ ውስጥ ድብርት እየተጫጫኖት፤ "እንዲሁ ተነስቼ መጮኽ ብጀምርስ?" ብለው አስበው ያውቃሉ። አልያም መኪናዎትን አስነስተው ለረጅም መንገድ እየነዱ ሳለ "ብጋጭስ" የሚል የድንገተኛ ሀሳብ በአእምሮዎ ሽው ብሎ ያውቃል?
እንዲህ ዓይነቶቹ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች "ድንገተኛ ረባሽ ሀሳቦች" ወይም በእንግሊዘኛው "intrusive thoughts" ተብለው ይጠራሉ። ብዙዎቻችን እንዲሁ በቀላሉ ችላ አንለዋለን እንጂ አልፎ አልፎ እንደዚህ ዓይነት ነገር ያጋጥመናል።
የተወሰኑ ሰዎች አእምሯቸውን በቀላሉ ከዚህ ዓይነቱ ሀሳብ ማውጣት ያቅታቸዋል። ወደ አእምሯቸው የሚመላለሱት ድንገተኛ ሀሳቦች ከልክ ወዳለፈ መብሰልሰል (obsessions) ይቀየራሉ። ይህም ወደ እርምጃ እንዲገቡ ወደሚያደርጋቸው አስገዳጅ ባህሪ ያመራል።
ዶ/ር ኒና ሂግሰን ስዊኒ ልጅ እያለች ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እስከምትመለስበት ጊዜ ድረስ "ጥሩ" ነገሮችን ብቻ ካላሰበች፤ ቤተሰቦቿ አንዳች ዓይነት ጉዳት እንደሚደርስባቸው ታምን ነበር።
"አንድ ድንገተኛ ረባሽ ሀሳብ ወደ አእምሮዬ ከመጣ ከባስ ማቆሚያው ጀምሮ እንደገና መራመድ እጀምር ነበር" ትላለች።
"መንገዱን እንደገና ሳልጀምር ቀርቼ የሆነ ነገር ቢፈጠር ጥፋቱ የኔ ነው የሚሆነው ብዬ የእውነት እፈራ ነበር" ስትል ታስታውሳለች።
ኒና 'ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር' የተባለው ጭንቀት የሚፈጥር፣ የማያባራ ረባሽ ሀሳብ ተጠቂ መሆኗ የተረጋገጠው በ10 ዓመቷ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ተመራማሪ ሆና የምትሠራው ኒና፤ በልጆች እና ታዳጊዎች የአእምሮ ጤና ላይ ትኩረት አድርጋ ትሠራለች።

የፎቶው ባለመብት, Dr Nina Higson-Sweeney
ኒና "መብሰልሰሎች (Obsessions) ድንገተኛ እና ያልተፈለጉ ሀሳቦች፣ ስሜቶች እና ግፊቶች ናቸው። አስገዳጅ ባህሪ (Compulsions) ደግሞ በመብሰልሰሉ ምክንያት የሚመጣን ጭንቀት ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ የሚከናወኑ ተደጋጋሚ እና ልማዳዊ ተግባራት ናቸው" ስትል ልዩነቱን ለቢቢሲ አብራርታለች።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዓለም ሕዝብ ከአንድ እስከ ሦስት በመቶ የሚሆነውን ኦሲዲ የተባለ የአእምሮ ጤና ችግር እንደሚጠቃ ይገመታል።
ድንገተኛ ረባሽ ሀሳቦች እጅግ አስጨናቂ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ሀሳቦች ብዙውን ጊዜ የሚያተኩሩትም ከግለሰቡ እሴቶች ወይም ማንነት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጩ ጉዳዮች ላይ ነው።
"የምትወጃቸው ሰዎች ሊጎዱ እንደሆነ የሚያሳስቡ ሀሳቦች ወደ አእምሮሽ ሊመጡ ይችላሉ" ትላለች።
"አንድ ሰው ወሲባዊ ዝንባሌውን መጠይቅ እንዲጀምር የሚያደርጉ ሊሆኑ ይችላሉ፤ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነኝ? ተቃራኒ ፆታን ነው የማፈቅረው? ብለሽ ልታስቢ ትችያለሽ። ሕጻናትን ለወሲባዊ ድርጊት የሚፈልግ ሰው ነኝ ብለሽ ጭምር እስከ መጨነቅ ድረስ ሊደርስ ይችላል" ስትል በምን ያህል መጠን ለግለሰቡ ማንነት ጋር ሊቃረኑ እንደሚችሉ ታስረዳለች።
ኒና እንደምትናገረው ብዙውን ጊዜ የተለመደው ድንገተኛ ሀሳብ በሽታ እንዳይተላለፍብን እንዲሁም ከህመም ጋር የተያያዘ ስጋት ነው።
ኦሲዲ በአብዛኛው የሚጀምረው በጉርምስና ወይም በታዳጊነት ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ኒና ትገልጻለች።
አንዳንድ ሰዎች ግን "ለዓመታት ጭንቀታቸውን ደብቀው ወይም ሸፍነው ሊቆዩ ስለሚችሉ" በሽታው የሚገኝባቸው ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ እንደሆነ ትናገራለች።
ኦሲዲ የሚፈጠርበት አንዱ ምክንያት ከዘረመል (ጄኔቲክ) ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ።
ሰዎች በልጅነት ዕድሜያቸው ባጋጠማቸው መጨቆን፣ የሞት ሐዘን እንዲሁም የቤተሰብ መበተን ምክንያት የሚፈጠር ጭንቀትም ለኦሲዲ መነሻ ሊሆን ይችላል።
የፀባይ ሥነ ልቦና ባለሙያዋ ኪምበርሊ ዊልሰን እንደምናገረው፤ ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ በሆነ ወቅት ላይ እንዲህ ዓይነት ድንገተኛ ረባሽ ሀሳቦች ያላጋጠመው የለም።
"ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 80 በመቶ የምንሆነው ሰዎች እነዚህ ሀሳቦች አጋጥመውናል" ስትል ታስረዳለች።
አብዛኞቹ ሰዎች እነዚህ ሃሳቦች በፍጥነት ማሳለፍ ይችላሉ። "ልንመለከታቸው፣ እንግዳ እንደሆኑ ልናስብ እና ወደ ጎን ልንተዋቸው እንችላለን" ትላለች።
ሀሳቦቹን ከአእምሮ ማጥፋት ካልቻሉ ግን እርዳታ መጠየቅ ሊኖርብዎት እንደሚችል የሥነ ልቦና ባለሞያዋ ትመክራለች።
"ከኦሲዲ ጋር የተያያዙ ሀሳቦች በቀላሉ አያልፉም፤ አእምሮ ውስጥ ይቀመጣሉ። ሁሌም ደግሞ በጎ ሀሳቦች አይደሉም፤ ኃይለኛ፣ ትንኳሽ እና ለመፍታት ቀላል ያልሆኑ ናቸው። ሁለ ነገርን የሚቆጣጠሩት እና ወደ አስገዳጅ ድርጊቶች የሚያመሩት የዚያን ጊዜ ነው" ስትል አብራርታለች።
የአስገዳጅ ድርጊቶች ምልክቶች እንደ አንድን ቁጥር ደጋግሞ መቁጠር ያሉ አእምሮ ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። አልያም ምንም ችግር እንደሌለበት የሚያውቁትን የመኪና ጎማ ደጋግሞ እንደመፈተሽ ያሉ የሚታዩ ተግባራት የመሆን ዕድል አላቸው።
ኦሲዲን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?
ዶ/ር ኒና፤ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም "ባለሙያ ወይም ስፔሻሊስት ምን ማድረግ ለአንቺ የተሻለ እንደሆነ ሊያስረዳ ይችላል" ትላለች።
ከባለሙያ እርዳታ በተጨማሪ ሰዎች ዕለት ተዕለት ጭንቀታቸውን ለመቀነስ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ዘዴዎች እንዳሉም ትናገራለች።
አንደኛው መፍትሔ ሃሳቦችን መለየት እና መሰደር ነው። " 'ድንገተኛ ረባሽ ሃሳብ እየመጣብኝ ነው' ብለሽ መለየት ሀሳቡን ለማራቅ እና ይሄ አንቺ እንዳልሆንሽ ለማስታወስ ይረዳል" ስትል ትገልጻለች።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ኦሲዲን እንደ የተለየ ነገር አድርጎ አዕምሯቸው ውስጥ መሳል ይረዳቸዋል።
"ኦሲዲ ምን እንደሚመስል መሳል ሊረዳ ይችላል፤ እኔ አለሁ፣ ኦሲዲ ደግሞ አለ፤ እነዚህም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው" ስትል ሌላ ዘዴ ትጠቅሳለች።
ራስን መንከባከብም ወሳኝ ነገር ነው። "ጥሩ ምግብ መመገብ፣ እረፍት እና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሊረዳ ይችላል። ምክንያቱም ስጨነቅ እና ራሴን ሳልንከባከብ ስቀር ሁልጊዜ ኦሲዲ ይብስብኛል" ትላለች።
ኒና አሁንም ከኦሲዲ ጋር የምትኖር ቢሆንም እንዴት መቆጣጠር እንደምትችል ግን ታውቃለች።
"መቼም ኦሲዲን አላጠፋውም፤ ነግር ግን ከእርሱ ጋር ሕይወቴን መቀጠል እችላለሁ። አሁን ላይ መጠነኛ በሆነ መልኩ ድንገተኛ ረባሽ ሀሳቦች ያጋጥሞኛል፤ እነሱንም እንዴት እንደምቆጣጠራቸው በደንብ እረዳለሁ። በምጨነቅበት ጊዜ ግን ሃሳቦቹን ማጥፋት ያስቸግራል፤ እናም አስገዳጅ ድርጊቶች ሊመሩኝ ይችላሉ" ስትል ለቢቢቢ አጋርታለች።














