ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለዓለም ዋንጫ ትኬት የገዙ ጎብኚዎች ለአሜሪካ ቪዛ 15,000 ዶላር ማስያዝ እንደማይጠበቅባቸው ተገለጸ
የዓለም ዋንጫን ለመመልከት ትኬት የገዙ ጎብኚዎች ለአሜሪካ ቪዛ 15,000 ዶላር ማስያዝ እንደማይጠበቅባቸው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አስታወቀ።
ከ50 አገራት የተውጣጡ የእግር ኳስ ወዳጆች ትኬት እስከገዙ ድረስ ለቪዛ ማስያዝ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ እንደማይከፍሉ ተገልጿል።
ከእነዚህ አገራት አምስቱ ማለትም አልጄርያ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሴኔጋል እና ቱኒዝያ ለዓለም ዋንጫ አልፈዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንጽላ ጉዳዮች ምክትል ጸሐፊ ሞራ ናምደር "ለዓለም ዋንጫ ትኬት የገዙ ተመልካቾች ለቪዛ ገንዘብ እንዳያሲዙ ወስነናል" ብለዋል።
ቀጣዩን የዓለም ዋንጫ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ ያስተናግዳሉ።
የአሜሪካ መንግሥት የቪዛ የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ጎብኚዎችን ቁጥር ለመቀነስ በሚል ቪዛ የሚያመለክቱ ሰዎች እስከ 15,000 ዶላር ማስያዣ እንዲያቀርቡ መወሰኑ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም እግር ኳስ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች ግን ገንዘብ ማስያዝ እንደማይጠበቅባቸው ተገልጿል። ተመልካቾችም ገንዘብ ማስያዝ እንደሌለባቸው የተገለጸው ደግሞ ትናንት ረቡዕ ነው።
አሜሪካ ባለፈው ነሐሴ ላይ የዘረጋችው ለ12 ወራት የሚቆየው የሙከራ ፕሮግራም፤ የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች ላይ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቪዛቸው ከሚፈቅድላቸው ጊዜ በላይ የሚቆዩ ሰዎችን ለመግታት በሚል የገንዘብ ማስያዣ መጠየቅን እንደ አማራጭ ወስዷል። ጎብኚዎች የቪዛ ቆይታ ጊዜያቸውን ሳያሳልፉ ከአሜሪካ ከወጡ ያስያዙት ገንዘብ ይመለስላቸዋል።
ፊፋ ከዋይት ሀውስ ጋር በመተባበር "ስኬታማ እና የማይረሳ ዓለም አቀፍ መሰናዶ" እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
"ይህ አስተዳደር በዘላቂነት ከጎናችን በመቆሙ ደስተኛ ነን" ሲል ተቋሙ መግለጫ አውጥቷል።
ለቪዛ ገንዘብ ማስያዝ የማይጠበቅባቸው 50 አገራት ዝርዝር ይፋ ቢደረግም ኢራን እና ሔይቲ አልተካተቱም። ከእነዚህ አገራት ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ተመልካቾች ገንዘብ ማስያዝ ቢጠበቅባቸውም፤ ውሳኔው እግር ኳስ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞችን እንደማይመለከት ተገልጿል።
ለዓለም ዋንጫ ካለፉ አገራት መካከል አይቮሪ ኮስት እና ሴኔጋል ክልከላው የሚተገበርባቸው በከፊል እንደሚሆንም ተመልክቷል።
የአሜሪካ መንግሥት ቱሪስቶች የአምስት ዓመታት የማኅበራዊ ሚዲያ ታሪካቸውን ማቅረብ አለባቸው የሚል ድንጋጌ ማውጣቱ አይዘነጋም።
የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የቪዛ ክልከላ፣ እስር፣ የጉዞ እገዳ እና ዘረኛ ውሳኔዎችን እንደሚያሰርጹ አስጠንቅቀዋል።