ኩባ ሙሉ በሙሉ ነዳጅ እንዳለቀባት ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኩባ ሙሉ በሙሉ ነዳጅ እና ናፍጣ እንደጨረሰች የኢነርጂ ሚኒስትሩ ቪሴንቴ ደ ላ ኦ ሌቪ ተናገሩ።

ከአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በጣም ውስን የጋዝ ክምችት ብቻ ቀርቷቸዋል።

አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ተከትሎ የኩባ የኃይል አቅርቦት "አደጋ ተጋርጦበታል" ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ትናንት በተለያዩ የሐቫና አካባቢዎች የኃይል መቆራረጥ ያማረራቸው ነዋሪዎች ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል።

አሜሪካ "የኩባ ኮምኒስት ሥርዓት ትርጉም ያለው መሻሻል ካሳየ" 100 ሚሊዮን ዶላር ለአገሪቱ እንደምትልክ በዚህ ሳምንት አስታውቃለች።

የኩባ ኢነርጂ ሚኒስትር "ድፍድፍ ነዳጅ አልቋል፣ ጋዝ አልቋል፣ ናፍጣ አልቋል። ደጋግሜ እየተናገርኩ ነው። የቀረን ጥቂት ጋዝ ብቻ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ በጣለችው ማዕቀብ ምክንያት በሐቫና ከ20 እስከ 22 ሰዓታት ድረስ መብራት እየጠፋ ይገኛል።

በአገሪቱ ያለው ሁኔታ "በውጥረት የተሞላ" መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሆስፒታሎች ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ሲሳናቸው ትምህርት ቤቶች እና የመንግሥት ተቋማት ተዘግተዋል።

ኩባ አገር ውስጥ ካሏት የነዳጅ ማጣሪያዎች በተጨማሪ አቅርቦት የምታገኘው ከቬንዝዌላ እና ሜክሲኮ ነበር። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ ግን ከሁለቱ አገራት ነዳጅ መሸመት አልቻለችም።

ትራምፕ ለኩባ ነዳጅ የሚሸጡ አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል። የኩባን ምጣኔ ሃብት የሚያንቀሳቅሰው የቱሪዝም ዘርፍም ተዳክሟል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር "አሜሪካ የ100 ሚሊዮን ዶላር ሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ ያቀረበችውን ጥያቄ ኩባ አልተቀበለችም" ብለዋል።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ሰብአዊ እርዳታው እንደሚከፋፈል አሜሪካ አስታውቃለች። ሆኖም ግን እርዳታው የሚሰጠው "ለውጥ ከታየ" መሆኑ ተመልክቷል።

"ውሳኔው የኩባ መንግሥት ነው። እርዳታችንን መቀበልም መተውም ይችላሉ። የኩባውያንን ሕይወት የሚታደግ እርዳታ እንዳይደርስ እያደረገ ያለው የአገሪቱ መንግሥት ነው" ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገልጿል።

አሜሪካ "የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል" ባለቻቸው የኩባ ባለሥልጣናት ላይ ያለፈው ሚያዝያ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪገዝ ማዕቀቦቹን "ሕገ ወጥ እና በዝባዥ" በማለት ኮንነዋል።