በኬንያ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን በመቃወም አደባባይ የወጡ ከ200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
የኬንያ ፖሊስ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን በመቃወም አደባባይ ከወጡ መካከል ከ200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታወቀ።
የናይሮቢ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢሳ ሞሐሙድ በመላ አገሪቱ የተጠራን የትራንስፖርት ማቆም አድማን ተከትሎ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል 225ቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።
በኬንያ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 10 2018 ዓ.ም. ከፍተኛ የነዳጅ ጭማሪን በመቃወም በመላ አገሪቱ የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች ሥራ አቁመው ውለዋል።
በናይሮቢ እና በዋና ዋና ከተማዎች የአውቶቡስ፣ የሞተር ሳይክል እና ሚኒባስ ትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ተጠቃሚዎች ረዥም ርቀት በእግራቸው ለመጓዝ ተገድደዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ተቃዋሚ ሠልፈኞች መንገድ ዘግተው ጎማ ሲያቃጥሉ ታይተዋል።
ፖሊስ መንገዶችን ለመክፈት በሚሞክርበት ወቅት ከተቃዋሚ ሠልፈኞቹ ጋር የተጋጨ ሲሆን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል።
የናይሮቢ ፖሊስ አዛዥ አምስት የፖሊስ እና አንድ የግለሰብ መኪኖች በሠልፈኞቹ መውደማቸውን አስታውቀዋል።
እስካሁን ድረስ በተቃውሞ ሠልፉ ምክንያት የሞተ ሰው ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።
ባለፈው ሳምንት የኬንያ ኢነርጂ እና ፔትሮሊየም ቁጥጥር ባለሥልጣን በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ውጥረት በመጥቀስ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ይፋ ካደረገ በኋላ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች በተለይ ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረቶች እና አሽከርካሪዎች የዋጋ ጭማሪው ለመስራት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል።
በተቃውሞ ምክንያት በርካታ የረዥም ርቀት ተጓዥ አውቶብሶች ጉዟቸውን በመሰረዛቸው የተነሳ መንገደኞች ተጉላልተዋል።
ዛሬ በኬንያ በነበረው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች ተቃውሞ የተነሳ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የንግድ ተቋማት ተዘግተው ውለዋል።
የአገሪቱ ገንዘብ ሚኒስትር ጆን ምባዲ የዓለም አቀፍ ነዳጅ ዋጋ ንረት በመካከለኛው ምሥራቅ ካለው ጦርነት ጋር እንደሚያያዝ ጠቅሰው ይህም በአገሪቱ ለተከሰተው ጭማሪ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ መንግሥት የታክስ እፎይታን ከግምት ሊያስገባ እንደሚችል ጨምረው አስታውቀዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች እና የተሽከርካሪ ባለቤቶች መንግሥት የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ቢጠይቁም እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል መግባባት ላይ አልደረሱም።