በፓኪስታን ወታደሮችን በጫነ ባቡር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ተገደሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፓኪስታን ውስጥ ወታደሮችን ሲያጓጉዝ የነበረ ባቡርን ዒላማ ባደረገ የቦምብ ፍንዳታ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለው፤ 70 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው።

ፍንዳታው የተፈጠረው ባቡሩ እሑድ ጠዋት ላይ በምዕራባዊው ባሎቺስታን ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ኩዌታ ውስጥ በሚገኘው የቻማን ፋታክ ባቡር ጣቢያ በሚያልፍበት ጊዜ ነው።

የባቡር መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ኡርዱ እንደተናገሩት፤ ከባቡሩ ውስጥ ሦስት ፉርጎዎች እና ሞተሩ አቅጣጫቸውን ስተዋል። ሁለት ፉርጉዎች ደግሞ ተገልብጠዋል።

ባቡሩ በዋነኛነት አገልገሎት ሲሰጥ የነበረው ለዒድ ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ወታደሮችን እና ቤተሰቦቻቸውን ለማጓጓዝ ነው።

ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂው 'ባሎቺስታን ሊብሬሽን አርሚ' የተባለው ተገንጣይ ታጣቂ ቡድን እንደሆነ የገለጸው የክልሉ መንግሥት፤ ጥቃቱም የተፈጸመው በአጥፍቶ ጠፊ ፍንዳታ መሆኑን አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት ይህንን ከማለቱ አስቀድሞ፤ ታጣቂ ቡድኑ ለጥቃቱ ኃላፊነት እንደሚወስድ ገልጿል።

ከፍንዳታ ስፍራ የወጡ ምስሎች ላይ የተቃጠሉ እና የወደሙ የባቡር ፉርጎዎች፣ አጠገብ የነበሩ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ጉዳት የደረሰበት በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሕንጻን ይታያል።

ናስር አህመድ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ "ፍንዳታው በተከሰተበት ወቅት ባቡሩ እየተንቀሳቀሰ ነበር፤ በውስጡም ተሳፋሪዎችም ነበሩ" ሲሉ ሁኔታውን ለቢቢሲ አስድቷል።

ክስተቱ ያጋጠመው እሁድ ጠዋት በመሆኑ ፍንዳታው በተፈጠረበት ሰዓት ቤተሰቦቹ ተኝተው እንደነበር የሚናገረው ናስር፤ የቤታቸው መስኮቶች በሙሉ እንደተሰባበሩ ገልጿል።

ፍንዳታው የተፈጠረው ፈንጂ የጫነ ተሽከርካሪ ወደ ባቡሩ ነድቶ ሲጋጭ እንደሆነ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

አንድ የፖሊስ መኮንን እና የባሎቺስታን ክልል ባለሥልጣን በጥቃቱ 20 ሰዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ኡርዱ አረጋግጠዋል። የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል። ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ ወታደሮች መሆናቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ "እንዲህ ያሉ የፈሪዎች የሽብር ተግባራት የፓኪስታንን ሕዝብ ቁርጠኝነት ሊያዳክሙ አይችሉም" ሲሉ ጥቃቱን አጥብቀው አውግዘዋል። "መላ አገሪቱ በዚህ የሀዘን ሰዓት ከባሎቺስታን ሕዝብ ጎን በአብሮነት ይቆማል" ብለዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማከም ሲባል ሆስፒታሎች ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት፤ ተጓዦቹ በአቅራቢያ ከሚገኘው ወታደራዊ የጦር ሰፈር ተነስተው ወደ ኩዌታ ዋና ባቡር ጣቢያ እያመሩ ነበር። ለበዓል ወደ ቤታቸው እየተጓዙ እንደነበረም አስረድተዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ባሎቺስታን ውስጥ ባቡር ላይ ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 'ጃፋር ኤክስፕረስ' የተባለው ባቡር ጣቢያ ለበርካታ ጊዜያት በታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞበታል።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ደግሞ ታጣቂዎች አንድ ባቡርን ጠልፈው በርካታ ተሳፋሪዎችን አግተው ወስደዋል።

'ባሎቺስታን ሊብሬሽን አርሚ' የፓኪስታን መንግሥት የባሎቺስታን ሕዝብን ተጠቃሚ ሳያደርግ በአገሪቱ ትልቅ በሆነው በዚህ ክልል ውስጥ ያለውን ሀብት እየበዘበዘ ነው የሚል ክስ ያቀርባል።

ከፓኪስታን አጠቃላይ የመሬት ስፋት ውስጥ 44 በመቶውን የሚይዘው ባሎቺስታን ክልል ነው። ክልሉ መረጋጋት ከራቃቸው የኢራን እና አፍጋኒስታን ድንበሮች ጋር የሚዋሰን ሲሆን የአረቢያን ባሕር የባሕር ዳርቻንም በከፊል ይዟል።

የካቲት መጀመሪያ ላይ በቡድኑ ተዋጊዎች እና በፓኪስታን የደህንነት ኃይሎች መካከል ኩዌታ እና በክልሉ ክፍሎች የተቀሰቀሰው ግጭት 31 ሲቪል ሰዎች ተገድለው ነበር።