አሜሪካ የገባችበት የኢራን ወደቦችን የመዝጋት ቁማር ሊሳካ ይችላል?

ዕሁድ ዕለት በኦማን አቅራቢያ በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዝ የታየ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዕሁድ ዕለት በኦማን አቅራቢያ በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲጓዝ የታየ መርከብ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካ ጦር ወደ ባሕረ ሰላጤው መርከቦች እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ የማድረግ አቅም እንዳለው ጥርጥር የለም። ጥያቄው ግን ምን ጠብ ለማድረግ ነው? የሚለው ነው።

ጡረታ የወጡ የአሜሪካ ባሕር ኃይል መኮንን አድሚራል ማርክ ማጋማሪ ለቢቢሲ "ሊሳካ ይችላል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል። "እናም በእርግጠኛነት ከሌላ አማራጮች በተሻለ መልኩ የሚደቅነው ስጋት አነስተኛ ነው፤ ይህም ኢራናዊያንን በኃይል ከመግፋት እና ለአጀባ አመቺ የሆነ ሁኔታ ከመፍጠር [የተሻለ ነው]" ይላሉ።

የኻርግ ደሴትን መቆጣጠር ወይም በሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚያልፉ መርከቦች ወታደራዊ አጀባ ማድረግን የመሰሉ የተለያዩ አማራጮች በዶናልድ ትራምፕ ሲነሱ ነበር። ይህ አይነት እርምጃዎች አደገኛ እና ዋጋ የሚያስከፍሉ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው።

በእነዚህ ዘመቻዎች የሚሳተፉ የአሜሪካ ኃይሎች ለኢራን ሚሳኤሎች፣ ድሮኖች እና ፈጣን ጀልባዎች ጥቃት እንዲጋለጡ ያደርጋል። በባሕር የተጠመዱ ፈንጂዎች ሌላ ተደራቢ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ።

በአንፃሩ እግዱ፤ የአሜሪካ የጦር መርከቦች በኦማን የባሕር ወሽመጥ ዳርቻ ሆነው ከአደጋ በራቀ ሁኔታ እንዲጠባበቁ እንዲሁም ከኢራን ወደብ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን እንዲከታተሉ እና እንዲያግዱ ይፈቅድላቸዋል።

"በወሽመጡ ውስጥ ካለው በጣም የተጣበበ አካባቢ በተሻለ አነስተኛ አደጋ ነው ያለው" ይላሉ አድሚራል ማጋመሪ።

ልዩ ኃይል፣ ሂሊኮፕተሮች እና ፈጣን ጀልባዎች ያሉት የአሜሪካ ባሕር ኃይል እንደዚህ ዓይነት ተልዕኮዎች ለመፈፀም የሚያስፈልገው ሁሉም መሣሪያዎችን ታጥቋል።

አቅሙን በቅርቡ ቬንዙዌላ እና ኩባ ላይ ባደረጋቸው እግዶች አሳይቷል። ባለፈው ጥር ደግሞ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በቁጥጥር ስር ያዋለው የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከብ እንደዚህ ዓይነት ተልዕኮዎችን በየትኛውም አካባቢ መፈፀም እንደሚችል ይመሰክራል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ኢራን ላይ የተጣለው እግድ "ያለ ልዩነት ወደ ኢራን ወደቦች እና የባሕር ዳርቻዎች በሚገቡ እና በሚወጡ የሁሉም አገራት መርከቦች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል" ብሏል። ነገር ግን ዕዙ የኢራንን ወደብ የማይጠቀሙ መርከቦችን እንደማያስቆም ገልጿል።

የሰብዓዊ ቁሳቁሶችን የጫኑ መርከቦች እንደሚፈቀድላቸው የጠቆመው ሴንትኮም፤ ነገር ግን ፍተሻ ይደረግባቸዋል ብሏል።

ይህ ሊሰራ ይችላል?

በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚኣልፉ መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, MarineTraffic

የምስሉ መግለጫ, ከእግዱ ከአንድ ቀን በኋላ በጣም ጥቂት መርከቦች በሆርሙሽ ወሽመጥ ሲያልፉ ታይተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአመክንዮ ደረጃ ግልፅ ይመስላል። ጦርነቱ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ ኢራን በባሕረ ሰላጤው የራሷን ፔትሮኬሚካል በስኬት ማዘዋወሯን ቀጥላለች። ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት ምርቶቻቸውን እንዳያንቀሳቅሱ በመከልከል የራሷን ምርት በመሸጥ ቢሊዮን ዶላሮችን አግኝታለች።

ውጤታማ የአሜሪካ ወደብ መዝጋት ይህን ፍሰት ያስቆማል። የኢራን አገዛዝ ክፉኛ የሚፈልገውን ገቢ ያሳጣል እንዲሁም ከዚህ በበለጠ ምጣኔ ሐብቱን ያዳክማል።

ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ በተፈጸመባት የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ከፍተኛ የመቋቋም አቅሟን ያሳየችው ኢራን፤ ሌላ ማዕበል ማሳለፍ እንደምትችል ሊሰማት ይችላል። በተለይም ደግሞ አዲሱ እግድ የነዳጅ ዋጋ ከዚህ በላይ እንዲጨምር ማድረጉ አይቀሬ ይመስላል።

የመካከለኛው ምሥራቅ የሰብዓዊ ጉዳዮች የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ዴቪድ ስታርፊልድ "ይህን ተሻግረው እንደሚያልፉ ያምናሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አሜሪካ በነዳጅ ዋጋ ጉዳቱ ይሰማታል፤ እናም የባሕረ ሰላጤው አገራት አሜሪካ ላይ ጫና በማሳደር በስተመጨረሻ ወሽመጡ እንዲከፈት ይወተውታሉ" ሲሉ ምን ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል።

ዋሽንግተን የኢራንን ንቅንቅ ያላለ ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ ማስገባት አለመቻሏንም ጠቁመዋል።

"ያሸነፉ መስሏቸዋል" ያሉት የቀድሞው ልዩ መልዕክተኛ፤ "ኢራናውያኑ ተቀናቃኛቸው ከሚችለው በላይ ጉዳት ለረጅም ጊዜ መቋቋም እንደሚችሉ ያምናሉ" ብለዋል።

የመርከብ ባለሙያዎች ከኢራን ወደቦች የሚወጡ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ የአሜሪካ እግድ ምን አይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚለውን ለመመልከት ዓይናቸውን ጥለዋል።

የባሕር ደኅንነት ተንታኝ የሆኑት ሚሼል ዋይዝ ቦክማን "አሁን በዚህ ቅፅበት የሚያልፉ መርከቦችን እየተመለከትኩ ነው። የባሕር ተጓዥ ብሆን ኖሮ በጣም ይጨንቀኝ ነበር" ብለዋል።

የመርከብ እና የጉዞ ጉዳዮችን የሚዘግበው ሎይድስ ሊስት ዋና አዘጋጅ ሪቻርድ ሜይድ በበኩላቸው "ትራምፕ በመጀመሪያ እግዱን ካሳወቁ በኋላ ወደመጡበት የተመለሱ [መርከቦች] አይተናል" ሲሉ ተፅዕኖውን ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እግዱን ከመጣላቸው ከ48 ሰዓታት አስቀድሞ የካቲት አጋማሽ ላይ ጦርነቱ ከመጀመረ ወዲህ ያልታየ የመርከቦች የትራፊክ መጨናነቅ እንደነበር ተናግረዋል።

"ለመውጣት የሚሞክሩ መርከቦች ግርግር ነበር" ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ባለው የተገደበ እንቅስቃሴ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ ወይም የሚወጡ መርከቦችን ሲይዝ ለማየት የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ ሊያስገድድ ይችላል። ወይም ከአነአካቴው ላይታይም ይችላል።

ለሁለት ሳምንታት የታወጀው የተኩስ አቁም ተፈፃሚነቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የኢራን ጦርነት በሁለት ተገዳዳሪ የመርከብ እግዶች ፍልሚያ ላይ ሲሆን፤ የዓለም ምጣኔ ሐብት ደግሞ በመሀል ተይዟል።

ቻይና በሳምንቱ መገባደጃ በኢስላማባድ በተደረገው የሰላም ንግግር ላይ ኢራን እንድትሳተፍ ሚና ተጫውታለች የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው። የዋሽንግተን አዲስ እርምጃ ቤጂንግ ተጨማሪ ጫና እንድታሳድር ያደርጋታል የሚል ተስፋ ይዛ ሊሆን ይችላል።

ቻይና የዓለማችን ትልቋ የኢራን ነዳጅ ገዢ አገር ናት። ምንም እንኳ ሰፊ እና ስልታዊ የመጠባበቂያ ማከማቻ ቢኖራትም በአቅርቦቷ ላይ የሚፈፀም መስተጓጎልን መቋቋም አትችልም።

የዶናልድ ትራምፕ ወቅታዊ እርምጃ ቁማር ነው። ተፅዕኖው ደግሞ በቅርቡ ይሰማል።