ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤልን የመከላከያ ሥርዓቶች የፈተኑት የሄዝቦላህ ድሮኖች
ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ወቅት ኦፕሬተሩ በቀጥታ እየተመለከተ የሚያንቀሳቅሳቸው (first-person view - FPV) አነስተኛ ድሮኖችን የሚጠቀምበት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል። ከእነዚህ ድሮኖች መካከል የተወሰኑት ቁጥጥር የሚደረግባቸው ፋየር ኦፕቲክ ኬብሎች ሲሆን ይህም ከውስብስብ የመከላከያ ሥርዓቶች ማምለጥ ያስችላቸዋል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ፤ የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ከመጋቢት 17/2018 ዓ. ም. ጀምሮ የለቀቃቸውን 35 ቪዲዮዎች መርምሯል።
ቪዲዮዎቹ፤ ሄዝቦላህ ደቡብ ሊባኖስ እና ሰሜን እስራኤል ውስጥ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ላይ የፈጸማቸውን ጥቃቶችን ያሳያሉ።
አነስተኛዎቹ ድሮኖች የራዳር የመለያ ሥርዓትን በቀላሉ ማለፍ ስለሚችሉ፤ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ውጤታማ የመከላከያ እርምጃዎችን ማዘጋጀት እንዳልቻለ" ባለሙያዎች ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ እንደሚያብራሩት፤ ድሮኖቹ በገበያ ላይ ከሚገኙ እና በ3ዲ ፕሪንተር ከተመረቱ አካላት ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው። ማውደም ከሚችሏቸው ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ዒላማዎች ጋር ሲነጻጸሩም የሚያስወጡት ገንዘብ ርካሽ ነው።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተስፋፋው ርካሽ የኤፍፒቪ ድሮኖችን የመጠቀም ልምድ፤ ዘመናዊ የውጊያ ስልትን ቀይሯል።
የእስራኤል ጦር ስለደረሰበት ጉዳት ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ አላደረገም። የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ግን በእነዚህ ድሮኖች አማካኝነት በተፈጸሙ ጥቃቶች አራት ወታደሮች እና አንድ ሲቪል ሰው ተገድለዋል፤ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል።
የእስራኤል ጦር፤ ድሮኖቹ የደቀኑትን አደጋ እንደሚገነዘብ እና የመከላከል አቅሙን ለማጎልበት፣ "ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የማስጠንቀቂያ ሞዴሎችን" ለማዘጋጀት እንዲሁም የወታደሮችን "ዝግጁነት እና ስለ ስጋቱ ያለቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ" እንዲቻል "ከፍተኛ ሀብት" እያፈሰሰ መሆኑን ለቢቢሲ ቬሪፋይ ገልጿል።
'ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ሴኪዩሪቲ ስተዲስ' የተባለው ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው፤ የእስራኤል ጦርም የኤፍፒቪ ድሮኖችን ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀም ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሊባኖስ እና በጋዛ በሐማስ ላይ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች እንደሚጠቀምባቸው ተቋሙ ገልጿል።
ወታደራዊ ተንታኝ እና የሊባኖስ ሠራዊት የቀድሞ ጄነራል የሆኑት ሂሻም ጃበር ለቢቢሲ አረቢክ እንደተናገሩት፤ ኤፍፒቪ ድሮኖችን "በራዳይ ላይለዩ" ይችላሉ። ሄዝቦላህ በክምችቱ የሚገኙትን "በመቶዎች የሚቆጠሩ" ይህ ዓይነት ድሮኖች በመጠቀም ታንኮችን ጨምሮ የተለያዩ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ማክሸፉን ያስረዳሉ።
ሄዝቦላህ ለበርካታ ዓመታት ትላልቅ የጥቃት ድሮኖችን በመጠቀም በሰሜን እስራኤል የሚገኙ ዒላማዎችን ሲመታ መቆየቱን የሚናገሩት ጃበር፤ አሁን የኤፍፒቪ ድሮኖች መጠቀም መጀመሩ "ፍጹም የተለየ ምዕራፍ" ውስጥ መግባቱን እንደሚያመለክት ገልጸዋል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ከመጋቢት 17 አንስቶ በሄዝቦላህ ቴሌግራም ቻናል ላይ የተለቀቁ 100 ገደማ የኤፍፒቪ ድሮን ጥቃቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን አግኝቷል። ከእነዚህ ውስጥ የ35ቱን ትክክለኛነት አረጋግጧል።
ሄዝቦላህ ግጭቱ ከጀመረበት የካቲት 23 በፊት ይህንን ዓይነት ጥቃት የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ይለቅቅ የነበረ አይመስልም።
ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን የተለቀቀ እና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ አንድ ቪዲዮ፤ ቢያንስ አራት የኤፍፒቪ ድሮኖች ኪርያት ሽሞና በተባለው አካባቢ አቅራቢያ በሚገኝ የእስራኤል የድንበር ካምፕ ላይ ተከታታይ ጥቃት ሲፈጽሙ እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በቅደም ተከተል ዒላማ ሲያደርጉ ያሳያል። ቢያንስ ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ወይም እንደወደሙ መመልከት ይቻላል።
ቢቢሲ፤ ታይበህ ከተማ ውስጥ የተፈጸሙ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶችን ጨምሮ በደቡብ ሊባኖስ የደረሱ ተመሳሳይ የድሮን ጥቃቶችን ተከታትሏል። ቪዲዮዎቹ ወታደሮች ዒላማ ሲደረጉ ያሳያሉ።
ቀጥሎ ደግሞ የቆሰሉ ወታደሮችን በማዳን ላይ የነበረ የእስራኤል ሄሊኮፕተር አቅራቢያ ሌላ ጥቃት ሲፈጸም ይታያል። በዚህ ጥቃት አንድ ወታደር እንደተገደለ እና ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከእነዚህ ድሮኖች ውስጥ አብዛኛዎቹ ሲበርሩ የነበሩት በሬዲዮ ወይም በሌላ ገመድ አልባ ሲግናል ሳይሆን በፋይበር ኦፕቲክ ኬብል ግንኙነት ነው። ይህ መሆኑም አሁን በሥራ ላይ ባሉ የእስራኤል ጥቃት መመከቻዎችን ተጠቅሞ መጠለፍን አደጋች ያደርገዋል።
በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የደኅንነት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንድሪያስ ክሬግ ለቢቢሲ ቬሪፋይ እንደገለጹት፤ ፋየር ኦፕቲክስ የእስራኤል የድሮኖች የመለየት እና የመጥለፍ አቅም "በአብዛኛው ጥቅም አልባ" ያደርገዋል። በተለይም ድሮኖቹን የሚያበርረውን ኦፕሬተር ፈልጎ ማግኘትም ይበልጥ አዳጋች እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ የእስራኤል ወታደሮች "ይበልጥ በጥንቃቄ እንዲንቀሳቀሱ፣ ይዞታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ እንደ መረብ እና የብረት ሳጥኖች ያሉ አካላዊ መከላከያ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ" እያስገደዳቸው ነው። ወዲያውኑ ለሚወሰድ አካባቢያዊ የመከላከያ እርምጃ የበለጠ ትኩረት መስጠት ግዴታ እንደሆነባቸውም ተናግረዋል።
ሄዝቦላህ ድሮኖቹን እንደ ቻይና ካሉ ቦታዎች የሚገቡ እና በገበያ ላይ በቀላሉ የሚገኙ የተለያዩ አካላትን ተጠቅሞ በሀገር ውስጥ የገጣጥሟቸው ሊሆን እንደሚችል የደኅንነት ባለሙያ ገልጸዋል። የአንዱ ድሮን ዋጋ ከ300 እስከ 500 ዶላር እንደሚገመትም አክለዋል።
በ 'ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሬዚሊያንስ' የመሣሪያ ባለሙያ እና ከፍተኛ መርማሪ የሆኔት ሊዮን ሃዳቪ እንደሚናገሩት፤ ከገበያ ላይ የተገኙት የድሮን አካላት 3ዲ ፕሪንተርን በመጠቀም በተመረቱ የመሣሪያ ክፍሎች ይደገፋሉ።
"በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ እና ባላቸው ወታደራዊ ያልሆነ አሠራር የተነሳ የእነዚህን ክፍሎች መገኛ መከታተል በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። በአብዛኛው እነዚህ የኤፍፒቪ ድሮኖች ደቡብ ሊባኖስ ውስጥ በበቂ ሁኔታ የሚገኘውን የአርፒጂ ተተኳሽ ጭንቅላት ይሸከማሉ" ሲሉ አብራርተዋል።
እጅጉን የተጠበቁ የሆኑት ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን አደጋ ላይ የጣሉት የኤፍቪፒ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸው በእስራኤል ወታደሮች ላይ ያሳደረው "ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ" ከፍተኛ እንደሚመስል ሃዳቪ ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ የተባባሰው የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ግጭት የተጀመረው አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከሁለት ቀናት በኋላ በመጋቢት 2/2018 ዓ.ም. ነበር።
አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሟቸው ተከታታይ ጥቃቶች የኢራንን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ገድለዋል። ሄዝቦላህ የኻሜኒን ሞት ተከትሎ እስራኤል ላይ ሮኬቶችን ተኩሷል።
እስራኤል በበኩሏ ሊባኖስ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም እና በአገሪቱን ደቡባዊ ክፍል እግረኛ ወታደሮችን በማሰማራት ምላሽ ሰጥታለች።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ 2,896 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህ ውስጥ ከ400 በላይ የሚሆኑት የተገደሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚያዝያ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረሙን ካወጁ በኋላ ነው። የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ የታጣቂዎችን እና የሲቪሎችን ሞት ለይቶ አላስቀመጠም።
ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን ተፈናቅለዋል። እስራኤል በበኩሏ በዚህ ግጭት አራት ወታደሮች እና 18 ንጹኃን መገደላቸውን ገልጻለች።