ጋና በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ዜጎቿን ማስወጣት ጀመረች

የጋና ባለሥልጣናት ረቡዕ ጠዋት ከደቡብ አፍሪካ ለመመለስ ከተመዘገቡ 800 ዜጎች ውስጥ የመጀመሪያው ቡድን እየተመለሰ መሆኑን አስታወቁ።
ቢቢሲ በደቡብ አፍሪካ ሰዓት አቆጣጠር ከማለዳው 3 ሰዓት አካባቢ በጆሃንስበርግ አየር ማረፊያ በጋና ኤምባሲ የተከራያቸው በርካታ አውቶቡሶች ተጓዦችን እያደረሱ እንደነበር ተመልክቷል።
ተመላሾቹ ወንዶች፣ ሴቶች እና በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናት ናቸው። በአነስተኛ ቡድን ደግሞ በፖሊስ መኪና የመጡ ተጓዦች እንደነበሩ ቢቢሲ ተመልክቷል።
ጋና ዜጎቿን እያስወጣች ያለችው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በደቡብ አፍሪካ ከተሞች የጸረ ስደተኞች ተቃውሞ ማዕበል መነሳቱን ተከትሎ ሲሆን፤ በአገሪቱ ውስጥ ዳግም የመጤ ጥላቻ ጥቃቶች ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍርሃት አለ።
የጋና መንግሥት ለቢቢሲ እንደተናገረው የመጀመሪያዎቹ 300 ሰዎች ረቡዕ ጠዋት ይጓዛሉ። ቀሪዎቹ የተመዘገቡ ዜጎችም እየተለዩ እንደሚጓዙ ገልጿል።
ለ10 ዓመታት በደቡብ አፍሪካ እንደኖረ እና የውበት ሳሎን ያስተዳደር እንደነበር የተናገረው ሩዶልፍ ከተመላሾች ውስጥ ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ በተነሱት ተቃውሞዎች ምክንያት ወደ አገሩ እየተመለሰ እንደሆነ ተናግሯል።
"ከዚህ በኋላ እዚህ መኖር የሚመች አይደለም። ስለዚህ መመለስ አለብን። በአገራችን ሰላም እንድናገኝ እመኛለሁ" ብሏል።
በደቡብ አፍሪካ 25 ሺህ የሚጠጉ ጋናውያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
የፀረ ስደኛ ተቃዋሚዎች ሕገ ወጥ ስደተኞች በሕዝብ አገልግሎቶች ላይ ጫና ማሳደራቸውን እና የአገሪቱ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
እነዚህን እንቅስቃሴዎች 'ማርች ኤንድ ማርች' ተብሎ በሚጠራ ቡድን የተዘጋጁ ሲሆን፣ ራሱን በዜጎች የሚመራ የኢምግሬሽን ለውጥ እንቅስቃሴ አድርጎ ይገልጻል።
ይህ ቡድን ሕገ ወጥ ስደተኞች እስከ ሰኔ 23 2018 ዓ.ም. ድረስ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ አውጥቷል።
ሩዶልፍ ይህ ቀነ ገደብ ወደ ኃይል ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ስጋት አለው።
"ተቃውሞዎቹ በደርባን ተጀመሩ፤ እና ወደ ሌሎች ግዛቶች ተስፋፉ። ስለዚህ መጥፎ ነገር ሊፈጠር ይችላል" ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ሩዶልፍ ዳግመኛ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደማይመለስም ተናግሯል።
የጋና ከፍተኛ ኮሚሽነር ቤንጃሚን ኳሺ ለቢቢሲ የዜጎቻቸው ደኅንነት እንዲጠበቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የጋና መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ የተሰማቸውን የዜጎቹን ድምፅ ሰምቷል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ዜጎቹን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ መጠበቅ የማንኛውም መንግሥት ግዴታ ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥ ስደተኞች ከጋና ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳይወጡ ለማድረግ ምን እየሰራችሁ ነው ተብለው ሲጠየቁ፣ ለተመላሾች የተቀናጀ ስትራቴጂ እንዳላቸው ተናግረዋል።
አንዳንድ ተንታኞች በደቡብ አፍሪካ ዳግም የተነሳው የስደተኞች ተቃውሞ በሚቀጥለው ኅዳር ከሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል።
እ.አ.አ በ2019 ቢያንስ 12 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ በ2008 ደግሞ በመላው አገሪቱ በተፈፀሙ ጥቃቶች 62 የውጭ አገር ዜጎች ተገድለዋል።
ነገር ግን የአዲሱ ተቃውሞ አዘጋጆች እንቅስቃሴዎቹ ሰላማዊ እንደነበሩ ይናገራሉ።
በዚህ ወር መጀመሪያ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሕገ ወጥ ኢምግሬሽንን መቆጣጠር አስፈላጊ እንደሆነ አምኖ፤ በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አውግዟል።















