ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች በኢቦላ ሕይወታቸው አለፈ
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሦስት የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደⶉች ከአስከሬን የተላለፈ ነው ተብሎ በተጠረጠረ ኢቦላ ሕይወታቸው አለፈ።
በጎ ፈቃደኞቹ መጋቢት 18 2018 ዓ.ም. በምሥራቃዊ የኢቱሪ ግዛት ከቫይረሱ ጋር ያልተያያዘ ፕሮጀክት ላይ ሲሰሩ በኢቦላን እንደተያዙ ይታመናል። ጊዜውም ቫይረሱ መሰራጨት መጀመሩ ከመታወቁ በፊት ነበር።
በጎ ፈቃደኞቹ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ሕይወታቸው አልፏል ተብለው የተለዩ የመጀመሪያዎቹ ተጎጂዎች ናቸው። በእስካሁን ቫይረሱ ከ170 በላይ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፤ 750 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው ተጠርጥረዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን በጎ ፈቃደኞቹ ማኅበረሰባቸውን "በጀግነነት እና በሰብዓዊነት" ካገለገሉ በኋላ እንደሞቱ ተናግሯል።
አሊካና ኡዱሙሲ አውጉስቲን፣ ሰዛቦ ካታናቦ እና አጂኮ ቻንዲሩ ቪቪያን የተባሉት ሟቾች በመንግዋሉ ከተማ ላይ ይሰሩ ነበር። ይህ አካባቢ አሁን የበሽታው ዋና ማዕከል ተብሎ ይቆጠራል።
በጎ ፈቃደኞቹ ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 8 2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ሕይወታቸው አልፏል።
የጤና ባለሙያዎች የኢቦላ ታካሚዎች ከሞቱ በኋላም ከአስከሬናቸው በሚወጣ ፈሳሽ በከፍተኛ ሁኔታ ቫይረሱን ማስተላለፍ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።
የዚህ በሽታ ስርጭት በደንብ በማይታወቀው "ቡንዲቡጊዮ" የተባለው የኢቦላ ዝርያ ምክንያት ይከሰታል። ይህም የተረጋገጠ ክትባት የሌለው እና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል ከሦስቱ አንዱን የሚገድል ነው።
አርብ ዕለት የዓለም የጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የተገኘውን ቫይረስ የማኅበረሰብ ጤና አደጋውን ከ"ከፍተኛ" ወደ "እጅግ ከፍተኛ" ከፍ አድርጓል።
የድርጅቱ ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱ በአፍሪካ ሰፋ ባለ ቀጣና አደጋ ከፍተኛ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን አደጋው ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
አጎራባች አገር የሆነችው ኡጋንዳ ቅዳሜ ዕለት ሦስት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል። ይህም በአገሪቱ በኢቦላ የተያዙ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር ወደ አምስት ከፍ አድርጓል።
የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ ማዕከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 10 አገራት በቫይረሱ ስርጭት አደጋ ላይ እንዳሉ አስጠንቅቋል።